አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ማይክሮሶፍት የኢትዮጵያን የዲጂታል ልማት ፕሮግራም መደገፍ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሄደ።
በኒውዮርክ 78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከማይክሮሶፍት ከፍተኛ አመራር ጋር በቴክኖሎጂ ትብብርና በጎ አድራጎት ስራዎች በኢትዮጵያና በማይክሮሶፍት መካከል ያለውን የጋራ ተጠቃሚነት በተመለከተ ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ እድገት፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና በተለያዩ ዘርፎች ላይ አሁን ያለችበትን ደረጃ በተመለከተ፤ በተለይም ስለ ዲጂታል እውቀትና ስልጠና ለኢትዮጵያ ወጣቶች ያለውን ጠቀሜታ አስመልክቶ ለአመራሩ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን የወጣት ኃይል እንዲሁም በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ኃይል ቁጥሯ ከፍተኛ ስለሆነ ማይክሮሶፍት ኢትዮጵያን ለሥራው ማዕከል አድርጎ እንዲመርጥና እድሎችን እንዲፈጥርም ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ያላትን ራዕይና በተለያዩ ዘርፎች እድገት፣ ፈጠራና ቅልጥፍናን ለማራመድ ያላትን አቅም አስረድተዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን የስነ-ምህዳር ጅማሬ እና ያላትን የፈጠራ አቅምን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
በዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ማይክሮሶፍት የኢትዮጵያውያን ጀማሪዎችን በገንዘብ፣ በማማከር ወይም መሳሪያዎችንና ግብአቶችን በማቅረብ መደገፍ በሚችልበት መንገድ ተወያይተዋል ሚኒስትሩ።
ሚኒስትሩ ስለዲጂታል አስተዳደርና የሳይበር ደህንነት ሲያብራሩ እንደገለጹት፥ ለአስተዳደርና ህዝባዊ አገልግሎቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል መድረኮች አስፈላጊነትን አብራርተዋል።
የማይክሮሶፍት ቴክኖሎጂ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ በሚችልባቸው የጋራ ሥራዎች፣ የሙከራ ፕሮጀክቶች ወይም መሰል ተነሳሽነት ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ወቅት ሁለቱ ወገኖች የትብብሩን አስፈላጊነት ደግመው የገለፁ ሲሆን ፥ በለጠ(ዶ/ር) ማይክሮሶፍት ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ያለውን ፍላጎት አድንቀዋል።
ለቀጣይ እርምጃዎች ከሁለቱም ወገን የስራ ቡድን በመመደብ ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመውሰድ በጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የማይክሮሶፍት አመራር ኢትዮጵያ ከማይክሮሶፍት ጋር አጋር ለመሆን ያላትን ፍላጎት በተመሳሳይ አድንቀዋል።
በመጨረሻም ሚኒስትሩ፥ ማይክሮሶፍት ኢትዮጵያን ለ’’ኒው ዲጂታል ልማት ፕሮግራም’’ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሦስት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ በማድረጉ አመስግነው፤ ማይክሮሶፍት በጥቅምት ወር አዲስ አበባን ለመጎብኘት ማቀዱን አድንቀዋል።