የሀገር ውስጥ ዜና

ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የተለያዩ ቅርሶች በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመለሱ

By Melaku Gedif

September 22, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ1868 በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የተለያዩ ቅርሶች በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመልሰዋል፡፡

ከተመለሱት ቅርሶች መካከል የመድሃኒዓለም ታቦት፣ የልኡል ዓለማየሁ የጸጉር ዘለላ፣ ከብር የተሰሩና በነሃስ የተለበጡ ሶስት ዋንጫዎች እንዲሁም በዘመኑ ጦርነት ላይ የዋለ የጦር ጋሻ ይገኙበታል፡፡

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑካን ቡድን ፣ የብሄራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ተወካይ፣ የብሪታኒያ ፓርላማ አባላት፣ ቅርሶቹን ለማስመለስ የተባበሩና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

አምባሳደር ተፈሪ መለሰ÷የተመለሱት ቅርሶች ለኢትዮጵያ ህዝብ ሃይማኖት፣ ታሪክ እና ባህላዊ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል፡፡

አሳዛኝ በሆነው የመቅደላ ጦርነት ምክንያት የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች እስካሁን አለመመለሳቸው በመላው ኢትዮጵያዊ ልብና አዕምሮ ውስጥ ጥያቄ ፈጥሮ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ ቅርሶች የአንድ ጥንታዊት ሀገር የታሪክ፣ የባህልና የማንነት መገለጫዎች ናቸው ማለታቸውንም የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡