አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ሊያክም የሚችል የወባ መድኃኒት ባለፉት ሦስት ወራት መሠራጨቱን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
እንዲሁም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ሊያክም የሚችል መድኃኒት በክምችት መኖሩን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን ንጉሴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት ባልተለመደ ሁኔታ የወባ ወረርሽኝ መከሰት የመድኃኒት ክምችት መጠኑን እንዳሳሳው አንስተው÷ የመድኃኒት ስርጭቱ ቀድሞ ከነበረው ከሦስት ዕጥፍ በላይ ጨምሯል ብለዋል፡፡
የግዥ ሂደቱን በማፋጠን የመድኃኒት አቅርቦቱ ሳይቆራረጥ እንዲቀርብ እየተደረገ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የታካሚዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰሎሞን÷ በጅማ ቅርንጫፍ በኩል በቂ መድኃኒት ስለተሰራጨ የአቅርቦት ዕጥረት አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ቅርንጫፎች መድኃኒቱን በንቃት ለጤና ተቋማት እያደረሱ ባለመሆናቸው የአቅርቦት መቆራረጥ ተከስቷል ነው ያሉት፡፡
ይሁን እንጂ ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ደሴ ለሚገኙ ቅርንጫፎች በአውሮፕላን ጭምር መድኃኒት ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ያረጋገጡት፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የወባ መድኃኒት ዕጥረት ባይኖርም ሰው ሠራሽ ዕጥረቶች ግን ፈተና ሆነውብናል ብለዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!