አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ) እና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት(ኦቻ) የኢትዮጵያን የሰላም ግንባታ ሂደት ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ከ78ተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በተጓዳኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴልና ከኦቻ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ደመቀ ለሩሴልና ግሪፊትስ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ለመተግበር፤ የመልሶ ማገገምና መልሶ ግንባታ ስራዎችን ለማፋጠን ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ገልጸዋል።
ዩኔሴፍ በኢትዮጵያ ለሕጻናት በትምህርትና ጤና ዘርፎች እያደረገ ያለውንም ድጋፍ ማድነቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በውይይቱ የኦቻ ኃላፊ በኢትዮጵያ የተቋረጠውን የሰብዓዊ እርዳታ ማስቀጠል ያለውን ፋይዳ አንስተዋል።
የዩኒሴፍና ኦቻ ኃላፊዎች ሁለቱ ተቋማት ለሰላም ግንባታ ሂደቱ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመሩትን ትብብር የመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ተመላክቷል።