አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሦስት ዞኖችን የሚያስተሳስረው የሃላባ-አንጋጫ-ዋቶ እና ዳምቦያ-ዱራሜ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት አፈጻጸም ከሚጠበቀው በታች መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ለግንባታው መጓተትም÷ የሥራ ተቋራጩ አቅም ማነስ፣ ከሕብረተሰቡ የቀረበ የዲዛይን ይሻሻልን ጥያቄ፣ የግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ መናር በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ባጋጠመ ችግር አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ከሚጠበቀው ደረጃ በታች መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ አመላክቷል፡፡
የመንገድ ግንባታው መጓተት በሕብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን በመገንዘብ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከሥራ ተቋራጩ አመራሮች ጋር ምክክር እያደረገ መሆኑን እና ሌሎች አማራጮችንም እያጤነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ስለሆነ ሕብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ አስተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
65 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሃላባ፣ ከምባታ እና ሃዲያ ዞኖችን የሚያስተሳስረው የመንገድ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን መካከል በተገባው ውል መሠረት በ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በጀት ታኅሳስ 2013 ወደ ግንባታ መገባቱ ይታወሳል፡፡