አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ርችት መተኮስ በፍጹም የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስገነዘበ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ÷ የመስቀል፣ የመውሊድና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ የጸጥታና የደህንነት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሀይል የሚመራ የጸጥታ ሀይል አጠቃላይ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱንም አንስተው፤ በዓላቱ በሰላም ተከብረው እንዲያልፉ ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በትብብር እንዲሰራ ጠይቀዋል።
በተለይ ህብረተሰቡ በመስቀል ደመራ በዓል ላይ የተከለከሉ ነገሮችን በፍጹም መያዝ እንደሌለበትና ለሚኖሩ ፍተሻዎች መተባበር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በየአካባቢው የሚደመሩ ደመራዎች አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ፣ ከዚህ በፊት ደመራ ተደምሮባቸው የማያውቁ ቦታዎች የጸብ መነሻ እንዳይሆኑ የድሮዎቹን መጠቀም እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በበዓላቱ ላይ ርችት መተኮስ በፍጹም ክልል መሆኑንም የተናገሩት ምክትል ኮማንደር ማርቆስ፤ ክልከላው የተደረገው ርችትን ሽፋን በማድረግ ህገወጦች ህገወጥ የጦር መሳሪያቸውን የሚሞክሩበት ጊዜ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ይህንን በመተላለፍ ርችት ሲተኩስ የተገኘ ግለሰብም ሆነ ተቋም በህግ አግባብ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሳፍንት እያዩ