አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለሚከበሩት የደመራ መስቀል፣ መውሊድ እና ኢሬቻ በዓላት የውሃና እና ኤሌክትሪክ አገልግሎቶች እንዳይቆራረጡ ዝግጅት መደረጉ ተመለከተ፡፡
በበዓላቱ ወቅት ለሚያጋጥሙ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ችግሮች ፈጥኖ የቅድመ መከላከልና መልሶ ግንባታ አገልግሎት ለመስጠት በቂ ዝግጅት ተደርጓል ተብሏል፡፡
በከተማዋ በአምስቱም የመግቢያ በሮች የመንገድ ላይ መብራት የምሰሶ ተከላ መከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ÷ ለበዓላቱ ከመደበኛ መስመሮች በተጨማሪ በቦቴ በቂ ውሃ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡
በበዓል ወቅት የሚከሰቱ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላልና ለመቆጣጠር በቂ ዝግጅት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን÷ ማሕበረሰቡም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ከጥንቃቄዎች አልፎ የእሳት አደጋ ካጋጠመ ነዋሪዎች በ939 እንዲሁም ለኤሌክትሪክ አደጋና መቆራረጥ በ905 እና ለውሃ መቆራረጥ በ903 በመደወል እንዲያሳውቁ ተጠይቀዋል፡፡