የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Shambel Mihret

September 26, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በዘንድሮው አመት 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ወንደሰን አቢ÷ በክልሉ እስከ መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው የምዝገባ ሂደት ውስጥ 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ተማሪዎችን ለመመዝገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም አስከ አሁን በክልሉ ከ4 ዞኖች ውጭ በ18 ዞኖችና በዞን ደረጃ ባሉ ከተማ አስተዳደሮች ከ49 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ከመጽሐፍ ጀምሮ የተለያዩ ግብዓት የማሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የ2016 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደትም በክልሉ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ከ326 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ወደ መማር ማስተማር ሂደት መገባቱን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አለምነው አበራ ገልፀዋል።

የትምህርት አመቱ የተሳካ እንዲሆን የግብዓት ማሟላት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን÷ ማህበረሰቡም ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።

በከድር መሀመድ