የሀገር ውስጥ ዜና

የመውሊድ በዓልን ስናከብር የትህትና መንገዶችን በማሰብ ሊሆን ይገባል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

By Alemayehu Geremew

September 26, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመውሊድ በዓልን ስናከብር የነቢዩ መሐመድን (ሰዐወ) በረከቶች በማስተዋልና የትህትና መንገዶችን በማሰብ ሊሆን ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ ትህትና፣ ደግነት እና ይቅር ባይነት ብዙዎቹን ችግሮቻችንን ይፈቱልናል፤ ብዙ ይቅርታዎች ብዙ ርቀት ወደፊት ያራምዱናል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነገ ለሚከበረው የነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

እንኳን ለመውሊድ በዓል አደረሳችሁ

ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች!

እንኳን ለየነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

መውሊደል ነቢ በሚከበርበት እለት፣ ሙስሊሞች መስጂድ ሄደው፣ በጋራ፣ ጸሎት ያድርጋሉ፡፡ የታላቁን ነቢይ ስራዎች፣ አስተምህሮቶች ይዘክራሉ፡፡ ነቢዩ በህይወት ሳሉ የነበራቸውን፣ ትህትና፣ ደግነት፣ ይቅር ባይነት ያስታውሳሉ፡፡ ከመስጂድ ከወጡም በኋላ፣ ያላቸውን ከሌላቸው ጋር በመካፈል፣ ለወገኖቻቸው ሁሉ ትሁት በመሆን፣ የበደላቸውን ይቅር በማለት፣ እንደ ዲናቸው መሪ፣ ትህትናን፣ ደግነትን እና ይቅር ባይነትን በተግባር ይፈጽማሉ፡፡

የየትኛውም እምነት ተከታዮች የሆንን እኛ ኢትዮጵያውያን፣ በዚህ ታላቅ በዓል ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር አንድ ሆነን፣ ትህትናን፣ ደግነትን እና ይቅር ባይነትን ገንዘባችን በማድረግ፣ መንፈሳዊ ህይወታችንን እናበለጽጋለን፡፡ አንድ ሆነን፣ በፍቅር እና በሰላም እናድጋለን፡፡ ትህትና፣ ደግነት እና ይቅር ባይነት የማይፈቱት ችግር የለም፡፡ የማያሻግሩት ወንዝ የለም፡፡

ውድ የእስልምና እምነት ተከታዮች እና መላ ኢትዮጵያውያን!

ይህን ታላቁን መውሊደል ነቢ ስናከብር ለሌሎች እምነት ተከታዮች፣ ወንዱ ለሴቱ፣ ትንሹ ለትልቁ፣ በሀገር ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ፣ የትም ላለው ኢትዮጵያዊ፣ ሁሉም ለሁሉም ትሁት ይሁን! ደግ ይሁን! በደልም ሲኖር፣ ይቅር ባይነት ይኑር!

ትህትና፣ ደግነት እና ይቅር ባይነት ብዙዎቹን ችግሮቻችንን ይፈቱልናል፡፡ ብዙ ይቅርታዎች ብዙ ርቀት ወደፊት ያራምዱናል፡፡

በየቦታው የሚነሱ አንዳንድ ችግሮችን እያየ፣ ሁሉ ነገር ጨለማ የሚመስለው ወገን አለ፡፡ ከየትኛውም ጨለማ በኋላ ግን ብርሀን አለ! ከየትኛውም ቋጥኝ እና ተራራ ባሻገር መንገድ አለ፡፡ ወንዙ፣ መሻገሪያ አለው፣ አቀበቱ ቁልቁለት አለው፡፡ ትሁት ብንሆን፣ ብርሀን ይታየናል፡፡ ደግ ብንሆን፣ መንገዱን እናገኘዋለን፡፡ ይቅር ባይ ስንሆን፣ መሻገሪያው ይታየናል፡፡

ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መልካም ነገሮችን ለማስተዋወቅ፣ መጥፎ ተግባራትን ሊቃወሙ የተሰጡ ናቸው፡፡ የሳቸውን አስተምሮ የሚከተል ሁሉ በዚህ ደረጃ ለመገኘት የሚደክም ነው፡፡ በጎ ነገሮች ተጓድለው ሲገኙ ወገኖችን ለማስተማርና ለመመለስ የሚደክም ነው፡፡