የሀገር ውስጥ ዜና

የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ተጠናቀቀ

By Meseret Awoke

September 26, 2023

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ12 ቀናት በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በስኬት መጠናቀቁን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ አስታወቁ፡፡

በማጠቃለያ መድረኩ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የስልጠናውን ማጠቃለያ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በሚመለከት የስራ ስምሪት መስጠታቸው ተገልጿል።

ስልጠናው የውስጠ ፓርቲ አንድነትን የበለጠ ያጠናከረ፣ አመራሩ እንዲማማርና ተሞክሮ እንዲለዋወጥ የረዳ መሆኑን አቶ አደም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የፓርቲውን መሰረታዊ እሳቤዎች መነሻ በማድረግ ተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት የተፈጠረበት መድረክ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ እቅዶቻችንንና ለሕዝብ ቃል የገባነውን በውጤታማነት እንድንፈፅም የሚያስችለን መድረክ ነው ብለዋል አቶ አደም፡፡ ለስልጠናው ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡