የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰጠው ድጋፍ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ

By Shambel Mihret

September 29, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰጠው ድጋፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተካሄደ፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ የቦርድ አማካሪዎች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ልምድ ለመቅሰምና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ልዑካን ቡድን አባላት ለኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰጠው ድጋፍ እያመጣ ያለው ለውጥ ላይም መክረዋል፡፡

በዚህም አባላቱ በቀጣይ ስለሚከተለው የድጋፍ ሁኔታና መንግስት ዘርፉን ለመደገፍ እየተከተለ ያለውን አቅጣጫ ለመገንዘብ ያለመ ውይይት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አመራሮችና አማካሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሂደትና አሁናዊ ሁኔታ፣ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ እየተከተለ ያለውን አቅጣጫና ዘርፉን የተሻለ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም የመጡ ለውጦችን በሚመለከት ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ልማት ባንክ በሚቀጥሉት ጊዜያት ስለሚያደርገው ድጋፍና መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ እየተከተለ ስላለው የፖሊሲ አቅጣጫ ገለፃ መደረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ልዑኩ የይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክንና የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንም ጎብኝቷል፡፡