አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እና የሩሲያው ሚቹሪንስክ የግብርና ዩኒቨርሲቲ የትብብር ሥምምነት ተፈራረሙ፡፡
የሥምምነት ፊርማውን የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) እና የሚቹሪንስክ ግብርና ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሰርጌይ ዢድኮቭ ተፈራርመውታል፡፡
በሥምምነቱ መሠረት ዩኒቨርሲቲዎቹ ዓለምአቀፋዊ እና ቀጣናዊ መርሐ-ግብሮችን በትብብር የሚተገብሩ ሲሆን፥ የተቋማቱ መምህራንና ተማሪዎችም የግብርና ምርት በሚያሻሽሉ ጥናቶች እና ምርምሮች ላይ በጥምረት እንዲሰሩ ያስችላል ተብሏል፡፡
ከዚህ ባሻገር በቤተ ሙከራ ሥራዎች እና በ”ግሪን ሐውስ” አሥተዳደር ዩኒቨርሲቲው ከሩሲያው ግብርና ዩኒቨርሲቲ መልካም ተሞክሮዎች ማግኘቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የሩሲያው የግብርና ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር ሰርጌይ ዢድኮቭ በበኩላቸው ÷ የሥምምነት ማዕቀፉ በሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የሰብዓዊነት ጉባዔ ላይ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጉዳዩ ላይ የተናገሩትን በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን የሩሲያው ግብርና ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ-ግብር ተማሪዎችን ከኢትዮጵያ ተቀብሎ ለማሰልጠን ቃል መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ