አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለሁለተኛ ዙር አስቸኳይ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ስርጭት መጀመሩን አስታወቀ፡፡
በኮሚሽኑ የሎጀስቲክስ ኦፕሬሽን ስራ አመራር ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ደምሴ እንዳሉት÷ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ ዜጎች የአስቸኳይ ድጋፍ እየቀረበ ነው፡፡
በመጀመሪያው ዙር ተመሳሳይ ድጋፍ ለሁሉም ክልሎች መሰጠቱን ጠቅሰው አሁንም መንግሥት ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ተደራሽ እያደረገ ነው ማለታቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዛሬው ዕለትም ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ፣ በቆሎ፣ የዳቦና የበቆሎ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ አልሚ ምግቦችና ከ1 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለሁለተኛ ዙር ተደራሽ የማድረግ ስራ ጀምረናል ብለዋል።
ድጋፉ ትግራይ ክልልን ጨምሮ ለተለያዩ ክልሎች አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ከ4 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተደራሽ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
ድጋፉ የሚሰራጨው ከአዳማ፣ ወላይታ፣ ሻሸመኔ፣ ሽንሌ፣ ኮምቦልቻና ድሬ ደዋ ካሉት የኮሚሽኑ መጋዘኖች ካለው ክምችት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ድጋፉ ከመጀመሪያው ዙር በመጠንና በአይነት መጨመሩን ገልጸው÷ ይህም የሀገሪቷ የእህል ክምችት መጨመሩን ያሳያል ነው ያሉት፡፡