ጤና

ከልክ ያለፈ ቁጣ የህፃናትን አዕምሯዊ እድገት እንደሚጎዳ ጥናቶች አመላከቱ

By ዮሐንስ ደርበው

October 05, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወላጆች፣ አስተማሪዎች፣ የህፃናት አሰልጣኞች እና ሌሎች ሰዎች በህፃናት ላይ የሚያሳዩት ከልክ ያለፈ ቁጣ የህፃናትን አዕምሯዊ እድገት እንደሚጎዳ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡

‘ቻይልድ አቢዩዝ’ በሚል ርዕስ በታተመ የጥናት ሰነድ በልጆች ላይ የሚደረግ ከልክ ያለፈ ቁጣ በህፃናት ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች ዝርዝር ውስጥ እንዲመደብ መደረጉ ነው የተገለፀው፡፡

አካላዊ ጥቃት፣ ስሜታዊ ጥቃት እና ፆታዊ ጥቃቶች ቀደም ሲል በህፃናት ላይ ይደርሳሉ የተባሉ እና በህግ የሚያስቀጡ ጥቃቶች ሲሆኑ በአዲሱ ጥናት ከልክ ያለፈ ቁጣም አራተኛ የህፃናት ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የጥናቱ ባለቤት ሻንታ ዱቤ÷ ወላጆች፣ መምህራን እና ታላላቅ ሰዎች በህፃናት ላይ የሚፈፅሙት ከልክ ያለፉ ቁጣዎችና ስድቦች በህፃናት ላይ የረጅም አመት የሚቆይ ተፅዕኖ አላቸው ብለዋል፡፡

እነዚህ ቁጣዎች እና ስድቦች ህፃናትን ለአዕምሮ ጭንቀት፣ ድብርት፣ ተናዳጅነት እና ቁጡነት ባህሪያት ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም በተፅዕኖ ውስጥ የሚያድጉ ህፃናት አደንዛዥ እፅ ተጠቃሚ የመሆን እንዲሁም በተለያዩ ወንጀሎች የመሳተፍ እድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ 2014 ባስጠናው ጥናት መሰረት በህፃናት ላይ የሚደርሱ አካላዊ እና ፆታዊ ጥቃቶች እየቀነሱ መምጣታቸው የተገለፀ ሲሆን በአንፃሩ በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ስሜታዊ ጥቃቶች ተባብሰዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ በህፃናት ላይ የሚደርሱ ከልክ ያለፉ ቁጣዎችን እና ስድቦችን ተፅዕኗቸውን እና መጠናቸውን በመለካት ህጋዊ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር ጠይቀዋል መባሉን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡