አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ጠቅላላ ስፋታቸው 546 ሺህ 200 ካሬ ሜትር የሆኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት መሠረተ ልማቶችም÷ የመንገድ አካፋይ፣ ዳርቻና አደባባይ፣ አረንጓዴ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም በግለሰብ የለሙ ሞዴል መንደሮች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና አበባ ለማድረግ የገባነው ቃል ወደ ተግባር መቀየራችን አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት የአረንጓዴ ልማት ሥራዎቹ ከተማዋን ውብ፣ ማራኪ፣ ፅዱ እና አረንጓዴ ከማድረግ በተጨማሪ ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል ነው ያሉት::
ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት በበጎ ፈቃደኝነት በትብብር የሰሩ ባለሃብቶችንና ያስተባበሩ አመራሮችን አመስግነዋል።