አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በማዕድን ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞች ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ለዘርፉ ማደግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለማዕድን አልሚ ደንበኞች ለማዕድን እና ግንባታ ግብዓት ስራ ማሳለጫ የሚያገለግሉ በ44 ሚሊየን ብር የተገዙ 15 ሎደር ማሽነሪዎችን በዛሬው ዕለት አስረክቧል፡፡
ባንኩ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ለማዘመን የተለያዩ የግብርና ማሽነሪዎችን በማስመጣት ለደንበኞቹ በማቅረብ ላይ መሆኑን በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በማዕድን ዘርፍ ለተሰማሩ ከ110 በላይ ደንበኞች ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ለማዕድን ልማት ዘርፉ ማደግ እየሰራ እንደሆነ መግለጹንም የባንኩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንሲንግ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው አበራ ÷ ባንኩ የማዕድን ዘርፍ ልማትን በመደገፍ ለሀገራዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ወርቅና የተለያዩ ማዕድናትን ለውጪ ገበያ በማቅረብ አበረታች ውጤቶች መታየታቸውን ጠቁመው ÷ይህም በዘርፉ ከተሰራ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አመላካች ነው ብለዋል፡፡