አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ሰሞኑን በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋድቤል ሙን እንደገለጹት÷ በቅርቡ ወንዞች ከመጠን በላይ ሞልተው ባስከተሉት የጎርፍ አደጋ የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በክልሉ ዘጠኙም ወረዳዎች በወንዞች አካባቢ የሰፈሩ ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።
በአደጋው ከ8 ሺህ በላይ ሄክታር ላይ በነበረ ሰብል፣ በ89 ትምህርት ቤቶች፣ በ43 የውሃና በሌሎችም የመሰረተ ልማት ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መንግሥት ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ፣ የፉርኖ ዱቄት፣ የዘይትና ሌሎች አልሚ ምግቦችን በድጋፍ ማቅረቡን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ምግብ ነክ ያልሆኑ እንደ የቤት መገልገያ ዕቃዎች፣ ፕላስቲክ ሸራዎች ፣አልባሳትን ያካተተ ድጋፍ እያቀረቡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በእስካሁኑ ሂደትም በላሬና በኢታንግ ልዩ ወረዳዎች ድጋፉ መድረሱንና ወደ ሌሎች ወረዳዎችም በመጓጓዝ ላይ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከጎርፍ አደጋው ጋር ተያይዞ በሰውና በእንስሳት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና እክሎችን ለመከላከልም የጤና፣ የውሃ፣ የትምህርት፣ የግብርናና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።