የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና ዩኒዶ የ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዮሮ የድጋፍ ሥምምነት ተፈራረሙ

By Tamrat Bishaw

October 06, 2023

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) የ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ሥምምነት ተፈራረሙ።

ድጋፉ ‘በልማት ምርቶች፣ አገልግሎቶች እና የግልና የመንግስት አጋርነት ወጣቶችን እና ሴቶችን መደገፍ’ በሚል ስያሜ ለሚተገበረው ፕሮጀክት ማስተግበሪያ የሚውል ነው ተብሏል።

ለፕሮጀክቱ ማስተግበሪያ የሚለው ገንዘብም በድርጅቱ በኩል ከጣሊያን መንግስት የሚመደብ በጀት መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

ፕሮጀክቱ መንግስት በስራ እድል ፈጠራ የተቋማትን አቅም በማጠናከር ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶችና ሴቶች ለማበረታታት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

ለሁለት አመታት የሚቆየው ይህ ፕሮጀክት በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል የሚተገበር ነው።

የድጋፍ ሥምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና የዩኒዶ ተወካይ እና ቀጠናዊ ዳይሬክተር ኦሬሊያ ፓትሪዢያ ካላብሮ ተፈራርመውታል።