አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ790 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቃሊቲ የአውቶብስ ዴፖ ዛሬ ተመረቀ።
የአውቶብስ ዴፖውን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በይፋ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
5 ነጥብ 2 ሄክታር ስፋት ያለው የቃሊቲ የአውቶብስ ዴፖ ማዕከል በውስጡ ለአውቶብሶች በቴክኖሎጂ የተደገፈ የጋራዥ አገልግሎት ፣ የእጥበትና የነዳጅ አቅርቦት እንዲሁም ዘመናዊ የአስተዳደር ህንጻ አለው።
በአንድ ጊዜ ከ250 እስከ 300 አውቶብሶች ከምድር በላይ እና 85 አውቶብሶችን ከምድር በታች መያዝ ይችላል።
በተጨማሪም 12 ዘመናዊ የመኪና ማጠቢያዎች፣ አራት ዘመናዊ የነዳጅ ማደያዎች እና ዘመናዊ ጋራዥ አለው።
የደህንነት ካሜራዎች የተገጠሙለት ዴፖው በአንድ ቦታ ስምሪት የሚሰጥ ማዕከልንም ይዟል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አወቀ ሀይሌ ዴፖው አስተዳደሩ በቀጣይ ለሚገዛቸው 3 ሺህ አውተብሶች አገልግሎት እንደሚሰጥ በምረቃው ላይ ተናግረዋል።
የአውቶብስ ዴፖውን በቀጣይ ለማስፋፋትም አጠገቡ ሁለት ሄክታር መሬት መከለሉንም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዴፖውን ከመረቁ በኋላ እንደተናገሩትም፥ የዛሬው ምረቃ የከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን የመጨረስ ግብ አንድ አካል መሆኑን አስታውዋል።
በከተማዋ አስተዳደሩ እየተገነቡ ያሉ እና የሚገነቡ ፕሮጀክቶች መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን በማንሳትም ለአብነት ዛሬ የተመረቀውን ዴፖ እና የሸገር ዳቦን ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቶች መጠነኛ ገቢ ያላቸው ያላቸው ዜጎችን ማእከል አድርገው መሰራታቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።
ይህም ስራ በኮቪድ -19 እና በሰሞነኛ የፖለቲካ አጀንዳዎች እንደማይስተጓጎልም ነው ያረጋገጡት።
በጥበበስላሴ ጀምበሩ