የሀገር ውስጥ ዜና

የምስጋና፣ የእርቅና የሠላም በዓል ከሆነው ኢሬቻ ብዙ ልንማር ይገባል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

By Tamrat Bishaw

October 06, 2023

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድነት የሚንፀባረቅበት የምስጋና፣ የእርቅና ሠላም በዓል ከሆነው ከኢሬቻ በዓል ብዙ ልንማር ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለመላው የኦሮሞ ህዝብ እንኳን ለኢሬቻ በዓል አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ኢሬቻ ከልዩነት ይልቅ አንድነት የሚንፀባረቅበት፣ የምስጋና፣ የእርቅና ሠላም በዓል መሆኑን ጠቅሰው፥ የኦሮም ህዝብ ጭጋጋማውን ክረምት ወቅት አልፎ በሰላም ወደ አዲሱና የብርሃን ተስፋ ወደያዘው ዓመት በሰላም ላሸጋገረ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

“ኢሬቻ የአንድነትና አብሮነት የሚጠናከርበት በዓል ነው፤ በዓሉ ካለው የሰላምና አብሮነት ግንባታ ዕሴት ትውልዱ ብዙ ሊማር ይገባል “ብለዋል ርዕስ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው።

ኢሬቻ በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረም ላይ የሚገናኝበት እንዲሁም ለዚህ ላደረሰ ለፈጣሪ በአብሮነትና ተሰባስበው ምስጋና የሚያቀርብበት መሆኑን አንስተዋል።

“በኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ለፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ በአንድነት ከመሰባሰቡ በፊት የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ቂምና ቁርሾ የሚተውበትና የተጣላ ይቅር የሚባባልበት ድንቅ የሆነ የሰላም ግንባታ ተምሳሌት በዓል ነውም “ብለዋል።

ኢሬቻ የልምላሜና ተስፋ አመላካች መሆኑን ያወሱት አቶ ደስታ፤ “ሁላችንም ከኢሬቻ በዓል ዕሴቶች ብዙ በመማር ያሉንን አቅሞች አሰባስበን ለልማትና እድገት መስራት አለብን ” ነው ያሉት።

ኢሬቻ ካለው የሰላምና አንድነት እንዲሁም የተስፋና ልምላሜ ዕሴት አንጻር ያለውን ጉልህ ሚና ለትውልድ ለማሸጋገር ልንጠብቀውና ልንንከባከበው ይገባልም ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ፤ እንኳን አደረሳችሁም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።