አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢሬቻ በዓል ምስጋናን፣ አብሮነትን፣ ይቅርታና እርቅን እንዲሁም ሰላምን ልንማር ይገባል ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል፡፡
የሆራ አርሰዴ የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ የአንድነት እና የወንድማማችነት ዓርማ” በሚል መሪ ሃሳብ በቢሾፍቱ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እየተከበረ ነው፡፡
ኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ተፈጥሮን ውብ አድርጎ የፈጠረውን ፈጣሪ የሚያመሰግንበትና የሚያከብርበት እንዲሁም ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁና መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪ የሚለመንበት በዓል ነው፡፡
የኢሬቻ በዓል የተጣላ ጸቡን በይቅርታ የሚሽርበት፣ የሰላም፣ የአብሮነትና የአንድነት እና የወንድማማችነት መገለጫ መሆኑንም ተሳታፊዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ተሳታፊዎች በዓሉን የተጣሉትን በሙሉ ልብ ይቅር በማለት፣ ሰላምን፣ አንድነትና ወንድማማችነት በማጎልበት እንደሚያከብሩ አንስተዋል፡፡
ስለሆነም ዜጎች እነዚህን የኢሬቻ መልካም እሴቶች በእለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴያቸው ላይ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ይቅርታ፣ ምስጋና፣ ሰላም፣ አብሮነትና መተሳሰብም የሕዝቦችን መግባባት፣ አንድነትና ወንድማማችነት ከማጽናት ባለፈ መልካም ግንኙነትም መፍጠር እንደሚያስችሉ አስረድተዋል፡፡
የአንድነትን፣ ይቅርታን፣ አብሮነትንና የወንድማማችነት እሴቶችን ማጎልበትም በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን ከስር መሰረታቸው ለማድረቅ ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ