የሀገር ውስጥ ዜና

በበጎ ፈቃድ ተግባር ወጣቶች በሰላም ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Shambel Mihret

October 08, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጀመረው የበጎ ፈቃድ ተግባር ወጣቶች ማህኅበራዊ እሴቶችን እንዲያዳብሩ በማድረግ በሰላም ግንባታ ተግባር የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት የ8ኛ ዙር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የስልጠና መርሐ-ግብር መክፈቻ ሥነ-ስርዓት በጅማ ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የሰላም የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ ሂሩት ድሌቦ÷ የበጎ ፈቃደኛ ተግባር አንድ ሰው የህሊናን ፈቃድ ተከትሎ ያለውን ማንኛውንም ነገር ያለስስት ለሌሎች መስጠት ነው ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለትውልድ በማስተላለፍ በዘር፣ በሃይማኖትና በሌሎች ማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን መከፋፈልና ጥርጣሬ በማስወገድ የወጣቶችን የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ለማሳደግ ሚናው የጎላ በመሆኑ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካይ ኤፍሬም ዋቅጅራ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ በመርሐ ግብሩ ዩኒቨርሲቲው የሰላም አምባሳደር መሆኑን ያስመሰከረበት ነው ብለዋል፡፡

ስልጠናው ከሀገሪቱ የተውጣጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ያሳተፈና የሰልጣኞቹን ክህሎት፣ ሥነ ምግባር፣ አመለካከት እንዲሁም የአካል ብቃት ግንባታንም የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡

ለአንድ ወር የሚቆየው ሥልጠና አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲገነዘብ በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር አስተሳሰብ ማሳደግን ያማከለ መሆኑ ተገልጿል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የሰላም ሚኒስቴርና የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኃላፊዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

በተስፋሁን ከበደ