አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሆራ ፊንፊኔና በሆራ አርሰዴ የኢሬቻ በዓል እሴቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ሀላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ የኢሬቻ በዓል በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ በትናትናው እለትና በዛሬው እለት የተከበረው የኢሬቻ በዓል እሴቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም ተከብሮ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
በዓሉ ትልቅ ትርጉም እንዳለው በመግለጽ በርካታ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት በዓል እንደሆነ አንስተዋል።
በዓሉ ከፍተኛ ታዳሚዎችን ቢያስተናግድም ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቆ ታዳሚዎች ወደየቀያቸው እየተለመሱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ በዓሉን ካከበረ በኋላ ሰላሙን ጠብቆ ወደየቀየው መመለሱ ለሰላም እሴት ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ማህበረሰብ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሆኖ ተጠናቋልም ነው ያሉት፡፡
በዓሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስት ፍሰትን የጨመረ፣ ኢኮኖሚውን ያነቃቃ እንዲሁም በርካታ ታዳሚዎች የተሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኢሬቻ በዓል ለህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ግንኙነትና የውስጥ አንድነትን ለማጽናት ወሳኝ በመሆኑ በዓሉን ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በዓሉ የኦሮሞ እሴትና ባህል ደምቆ የታየበት መሆኑን ጠቅሰው÷ ከሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች የተውጣጡ ታዳሚዎች የተሳተፉበት ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ ታዳሚዎች መጥተው የኦሮሞ ህዝብ ባህል ባህሌ ነው በማለት ያደመቁበት በመሆኑ ትልቅ ትርጉም እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ በክልሉ ስም ምስጋና አቅርበዋል።