ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ ጦሯን ወደ እስራኤል ማስጠጋቷ ተሰማ

By Mikias Ayele

October 09, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃማስ በደቡባዊ እስራኤል ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ አሜሪካ ጦሯን ወደ እስራኤል ማስጠጋቷ ተሰምቷል፡፡

የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት እንዳስታወቀው÷ የሃማስን ጥቃት ተከትሎ ዋሺንግተን  የአውሮፕላን ተሸካሚዎችን፣ መርከቦች እና ተዋጊ ጄቶችን ወደ ምሥራቅ  ሜዲትራንያ ባህር እያንቀሳቀስች ነው፡፡

ወታደራዊ እንቅስቃሴው የሃማስን ጥቃት ለመከላከል እና ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሃማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት “በሀገሪቱ ተከስቶ የማያውቅ  አሰቃቂ ድርጊት” ሲሉ ማውገዛቸው  ይታወሳል፡፡

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሄም ራይሲ በበኩላቸው ÷እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና አደጋ እየጣለች ነው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡

ሃማስ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ ጥቃት የፈፀመው ከኢራን ባገኘው ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ድሮኖች መሆኑ ቢገልፀም÷አሜሪካ ግን በጉዳዩ ላይ ማስረጃ አላገኘሁም ማለቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ይሁን እንጂ  ኢራን ላለፉት ዓመታት ለሃማስ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷ ግልጽ  ነው ሲሉ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስታውቀዋል፡፡፡፡

ሃማስ ያለ ኢራን ሁለንተናዊ ድጋፍ ሃማስ ሆኖ ይቀጥል እንዳልነበርም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡