የሀገር ውስጥ ዜና

ምክር ቤቱ የፊሲካል ፌዴራሊዝምን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ

By Feven Bishaw

October 09, 2023

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሀገሪቱን የፊሲካል ፌዴራሊዝም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እየሠራ መሆኑን በምክር ቤቱ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገልፀዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የ2016 የበጀት ዓመት እቅድን በተመለከተ ከክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ጋር እየተወያየ ነው፡፡

በዚህ ወቅት አቶ ሽመልስ÷ከለውጡ በፊት ስለጋራ ገቢዎች ክፍፍልና ስለመሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሐዊነት በግልጽ የመወያየት ባህል እንዳልነበረ አስታውሰው አሁን ግን በፌዴራልና በክልሎች መካከል የሚከፋፈሉ የጋራ ገቢዎች፣ የድጎማ በጀቶችና በፌዴራል ተቋማት ለክልሎች የሚሰራጩትን የመሠረተ ልማት አውታሮች በፍትሐዊነት እና በውጤታማነት ተደራሽ ለማድረግ ግልፅ የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶላቸው እንዲፈጸሙ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ምክር ቤቱ የፊሲካል ሽግግሮችን ፍትሐዊና ውጤታማ ሊያደርጉ የሚያስችሉ የተለያዩ ጥናቶችና ምርምሮችን መነሻ ያደረገ የዐሥር ዓመት መሪ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቱን መናገራቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የ2016 የበጀት ዓመት እቅድን ለኮሚቴው አባላት ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ በበኩላቸው÷ ምክር ቤቱ የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊና ውጤታማ እንዲሆን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሕዝቦች ሕገመንግሥታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ለማስተናገድና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ተቋማዊ ሪፎርም ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ ለምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡