የሀገር ውስጥ ዜና

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ የተሻለች ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ዕድል ዕጃችን ላይ ነው ሲሉ አስገነዘቡ

By ዮሐንስ ደርበው

October 09, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀደሙ ክፍተቶችንና ዝንፈቶችን በማረም ወደ ፊት ዕድላችንን ተመካክረን በማቅናት የተሻለች ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ዕድል ዕጃችን ላይ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ አስገነዘቡ፡፡

በ6ኛው የሁለቱ ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ – ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ÷ “ያደሩና ለዘመናት የነበሩ የሐሳብ ልዩነቶችን ለማስታረቅ እና ለማቀራረብ ብሎም ወደ ተሻለ መግባባት እንዲወስደን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁመናል” ብለዋል፡፡

የቀደሙ ክፍተቶችንና ዝንፈቶችን በማረም ወደ ፊት ዕድላችንን ተመካክረን በማቅናት የተሻለች ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ዕድል ዕጃችን ላይ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ውይይት ሁሉን አሸናፊ ያደርጋል ያሉት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ÷ አለመግባባቶችና ጥያቄዎች ሁሉ በንግግር ሲፈቱ ድሉ የሁላችንም መሆኑን መረዳት ይገባል ነውያሉት፡፡

በየትኛውም አካባቢ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች እና ግጭቶችን በማቆም የሰላም አማራጮችን ከመጠቀም ውጭ የተሻለ አማራጭ እንደሌለን መገንዘብ ያስፈልጋል ሲሉም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

በተደጋጋሚ በታሪካችን ውስጥ እንዳመለጡን ዕድሎች ይህ ዕድል ሊያመልጠን አይገባም ያሉት ፕሬዚዳቷ÷ አንድ ነባር ክፉ ልማድ አለን ዕድሎች በዕጃችን እያሉ እንደዋዛ እናሳልፋቸዋለን፤ ከዘመናት በኋላ እንቆጭባቸዋለን ብለዋል፡፡

ምክክሩ ያጠፋናቸውን ለማረም፤ ያልተግባባነውን ለማግባባት፤ የተሠበረውን ለመጠገን፤ የተጣመመውን ለማቃናት፤ የተራራቀውን ለማቀራረብ፤ ዳርና ዳር ያለውን ወደ መሐል ለማምጣት እና ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ለመገንባት ተማምነን መሠረት የምንጥልበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የቅድመ ዝግጅት ሥራውን ማጠናቀቁን እና በዚህ ዓመት ወደ ምክክር ምዕራፍ እንደሚሻገርም ነው ያስታወቁት፡፡

ምክክሩ ልዩነትታችንን ማጥበበቢያ ነው፤ አብሮነታችንን አጉልተን በሀገረ- መንግሥት ግንባታችን ሂደት የታዩ መሠረታዊ ስብራቶችን የምናክምበት ዕድል ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሁላችንንም መስላ፤ በሁላችንም እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ በአስተማማኝ መሠረት እንድትታነጽ የሚያስችለን ልዩ አጋጣሚ ነው፡፡

ኮሚሽኑ የተጣለበትን ተስፋ ዕውን እንዲያደርግ የሁላችንም ንቁ ተሳትፎ ያስፈልገዋል ነው ያሉት፡፡

መነጋገር፤ መከራከር፤ መግባባት የዚህ ትውልድ ኢትዮጵያውያን መለያ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በዮሐንስ ደርበው