የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል የቤት ለቤት ዘመቻ ሊካሄድ ነው

By Meseret Awoke

October 10, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የወባ በሽታን በመከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ የቤት ለቤት ዘመቻ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ።

በጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራም ባለሙያና አስተባባሪ አዲሱ ጦና ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፥ ዘመቻው ከፊታችን ጥቅምት 10 ጀምሮ ይከናወናል፡፡

በክልሉ በተለያዩ ዞንና ወረዳዎች በገጠር ቀበሌዎች ጭምር የወባ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ዘመቻ ከ15 ቀናት በላይ እንደሚካሄድም ነው የገለጹት።

በዘመቻው የቤት ለቤት ምርመራና ማከም፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በኬሚካል የማፅዳትና የመድፈን ስራን እንዲሁም በወባ መከላከል ዙሪያ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመስጠት ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በአሁን ወቅት የወባ በሽታን ለመከላከል በ4 ሆስፒታሎች፣ በ29 ጤና ጣቢያዎች በ140 ጤና ኬላዎች የምርመራና የህክምና ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉም ነው ያሉት አቶ አዲሱ።

በተለይም በአሁን ወቅት የሚስተዋለውን የወባ በሽታን ለመከላከል በጤና ሚኒስቴር በኩል በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ 37 ሺህ 500 ያህል አጎበሮች ለማህበረሰቡ የማሰራጨት ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

ሆኖም አጎበር ያልተዳረሰባቸው መኖሪያ አካባቢዎች እንዳሉ ጠቅሰው፥ በቀሪ አካባቢዎች አጎበር ለማዳረስ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በታሪክ አዱኛ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!