የሀገር ውስጥ ዜና

በአቶ አብነት ገ/መስቀል የ1 ሺህ 971 ካሬ ሜትር የይዞታ ሽያጭ ጋር ተያይዞ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለፖሊስ የ10 ቀን ጊዜ ተሰጠ

By ዮሐንስ ደርበው

October 10, 2023

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በባለኃብቱ አቶ አብነት ገ/መስቀል የ1 ሺህ 971 ካሬ ሜትር የይዞታ ሽያጭ ጋር ተያይዞ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለማጣሪያ ምርመራ ለፖሊስ የ10 ቀን ጊዜ ተሰጠ።

ተጠርጣሪው አቶ አብነት በቂርቆስ ክ/ከ ወረዳ 2 የሚገኘውን ከሼክ አላሙዲን መሀመድ ጋር የጋራ ንብረት የሆነ የ1 ሺህ 971 ካሬ ሜትር ይዞታ በመሸጥ ለግል ጥቅም አውለዋል ተብለው ተጠርጥረው ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ መርማሪ ፖሊስ ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄን በሚመለከት የተጠርጣሪ ጠበቆች ጉዳዩ ከዚህ በፊት ምርመራ ሲደረግበት የቀረበና ዳኝነት የተሰጠበት ጉዳይን እንደ አዲስ ምርመራ ተብሎ መቅረቡ አግባብ አይደለም በማለት የተከራከሩና ከዚህ በፊት የነበረው የምርመራ መዝገብ ይታይልን በማለት ጠይቀው ነበር።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቶ አብነት በተጠረጠሩበት ወንጀል ፖሊስ ባቀረበው ምርመራ የማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ መነሻ እና የተጠርጣሪ ጠበቆች የተነሳ መከራከሪያን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ በቀጠረው መሰረት ተሰይሟል።

ተጠርጣሪው አቶ አብነት ከአራት ጠበቆቻቸው ጋር በችሎት ቀርበዋል።

በዚህ መሰረት ፍርድ ቤተ ከዚህ በፊት የተደረገው ምርመራ በቂርቆስ ክ/ከ ወረዳ 1 ከነበረ የ3 ሺህ 383 ካሬ ሜትር ይዞታ ሽያጭ ጋር ተያይዞ የአሁኑ የሚመሳሰል አለመሆኑንና አሁን ፖሊስ የጠየቀበት በወረዳ 2 ስር የሚገኝ የ1 ሺህ 971 ካሬ ሜትር የይዞታ ሽያጭ ጋር ተያይዞ መሆኑን በመጥቀስ የመከራከሪያ መቃወሚያቸውን አለመቀበሉን ገልጿል።

ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የምስክር ቃል ገና ያልተቀበለ መሆኑን ተከትሎ ተጨማሪ የማጣሪያ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ማመኑን ጠቅሶ ጠበቆች የጠየቁት ዋስትና ጥያቄን ለጊዜው አለመቀበሉን በማብራራት ለፖሊስ የ10 የምርመራ ማጣሪያ ቀን ፈቅዷል።

በዚህ ጊዜ የአቶ አብነት ጠበቆች ከዚህ በፊት በሐምሌ ወር በጉዳዩ ላይ ምርመራ መደረጉን ዐቃቤ ህግ ገልጾ ከሀገር እንዳይወጡ እግድ ተጠይቆበት ዳኝነት ተሰጥቶበታል ያሉትን ሰነድ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትላቸው በመጠየቅ ሰነዱን በችሎት አቅርበዋል።

የጊዜ ቀጠሮ ዳኞቹ ለደቂቃዎች ከችሎት ወጥተው በጽ/ቤት ሰነዱን ተመልክተው ተወያይተው በመመለስ በመዝገብ ቁጥሩ በተጠቀሰበት ሰነድ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ ተደርጓ የተጣራ ነገር ስለመኖሩ አያሳይም በማለት የጠበቆቹን አቤቱታ አለመቀበሉን በመግለጽ አስቀድሞ ለፖሊስ የሰጠውን የ10 ቀን ምርመራ ማጣሪያ ጊዜ አጽንቶታል።

የፖሊስን የምርመራ ውጤት ለመጠባበቅ ለጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጥሯል።

አቶ አብነት ገ/መስቀል የቦሌ ታወር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጅምር ግንባታ ያለበት 3 ሺህ 383 ካሬ ሜትር ይዞታን ያለአግባብ ባለመብት በመሆን ይዞታው ላይ ካርታ በማውጣት ከ321 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሸጥ አድርገዋል ተብለው ከሌሎች ከመሬት አስተዳደር ሰራተኞች ጋር በ2ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ላይ ዋስትና እንደተፈቀደላቸው ከአንድ ወር በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ