የሀገር ውስጥ ዜና

በፍልሰት ጉዳዮች በቅንጅት መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ውይይት ተደረገ

By ዮሐንስ ደርበው

October 10, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና በቀጣናው ስላለው የፍልሰት ጉዳዮች ላይ በቅንጅት መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት መደረጉን ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ከዓለም ዓቀፉ የፍልሰት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኤሚ ኢ. ፖፕ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ፍልሰትን ለመቀነስ በክኅሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ማስፈን ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ መምከራቸውን ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪም የዓየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ተወያይተናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጣናዊ የሚኒስትሮች ፎረም ላይ እያበረከተችው ስላለው አስተዋጽኦም መምከራቸውን አንስተዋል፡፡

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪቱን ለማቀላጠፍ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ይበልጥ ስለሚሰፋበት ሁኔታ መወያየታቸውንም ነው ሚኒስትሯ ያመላከቱት፡፡

ድርጅቱ በፍልሰት፣ ክኅሎት ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት ላሳየው ቁርጠኝነትም አመስግነዋል፡፡