አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን መለየት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) ዛሬ በሠመራ ከተማ በሰጡት መግለጫ÷ ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ የክልሉን ተወካዮች ለመምረጥ መድረክ እንደሚያካሄድ ተናግረዋል።
በመድረኩ 432 ተባባሪ አካላት የሚሳተፉበትና ተወካዮቻቸው በብቃትና በገለልተኝነት እንደሚመርጡ የሚመቻች መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይ ምዕራፍ የተሳታፊዎች ልየታ በመምራትና በማስተባበር የሂደቱን ውጤታማነት እንደሚከታተል የገለጹት ኮሚሽነሯ፥ ከ48 ወረዳዎች የተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አጀንዳ ለማሰባሰብ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ ብለዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ አመቺነት የሀገር የጎሳ መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራንና የንግዱ ማህበረሰብ በሂደቱ እንደሚሳተፉ ኮሚሽነሯ አመልክተው ከየወረዳው 10 ሰዎች በአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት እንደሚወከሉ ተናግረዋል።
በተሳታፊ ልየታ ሂደት ላይ የጎሳ መሪዎችና ሐይማኖት አባቶች፣ የክልሉ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች፣ የወረዳ ፍርድ ቤትና የሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የመምህራን ማህበር፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች በተባባሪነት እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።
የክልሉ ነዋሪዎች ለሂደቱ መሳካት ይበጁኛል የሚሏቸውን ወኪሎች በተወካዮቻቸው አማካይነት እንዲያቀርቡ ጥሪ መቅረቡን ኢዜአ ዘግቧል።