አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመረጣቸው ሕዝብ አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ውክልናቸውን ማንሳት በሚቻልባቸው ሒደቶች ላይ ረቂቅ መመሪያ አዘጋጀ።
ዜጎች በመረጡት ተወካያቸው ላይ አመኔታ የሚያጡ ከሆነ የይውረድልን ጥያቄ ማቅረብ የሚችሉበት ረቂቅ መመሪያ ላይ የፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች ውይይት በማካሄድ ላይ ናቸው።
በውይይቱ ወቅት የቀረበው ረቂቅ መመሪያ የተፈጻሚነት ወሰንም ህዝቡ ለፌዴራል እና ለክልል ምክር ቤት በመረጠው ተመራጭ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ የይውረድልን ጥያቄ የምክር ቤት አባሉ በተመረጠበት ዓመት እና በመጨረሻው ዓመት መቅረብ እንደማይችልም ነው የተነገረው።
ነገር ግን በቦርዱ ተቀባይነት በሚያገኝበት ልዩ ሁኔታ ብቻ በመጀመሪያው ዓመት በተወካዩ ላይ የይውረድልን ጥያቄ ማቅረብ የሚቻል መሆኑም በረቂቅ መመሪያ ላይ ተጠቁሟል።
ጥያቄው ሊቀርብ የሚችለው አንድ የምክር ቤት አባል በተወዳዳረበት የምርጫ ክልል ሲሆን ፥ ከ100 በላይ መራጮች ተፈራርመው ጥያቄውን ማቅረብ እንደሚችሉም ነው የተብራራው።
ጥያቄውን የሚያቀርቡ መራጮችም በዋናው ምርጫ ወቅት በምርጫ ጣቢያ የተመዘገቡ መሆን እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።
በሚያቀርቡት ሰነድ ላይ በተመራጩ ላይ አመኔታ ስላጡበት ምክንያት በግልጽ ማመልከት እንደሚኖርባቸውም ነው የተነሳው።
ጥያቄው በቦርዱ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነም ቦርዱ ጥያቄውን ላቀረቡ አካላት በምርጫ ክልሉ የሚገኙ ከ15 ሺህ በላይ መራጮች ስለመስማማታቸው የሚያስፈርሙበት ወረቀት እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል።
በዚህም ማስፈረሚያ ወረቀት ላይ መመዝገብና መፈረም ያለባቸው ግለሰቦች በዋናው ምርጫ ወቅት በምርጫ ጣቢያዎች ለመምረጥ የተመዘገቡ መሆን እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።
ፊርማው ለቦርዱ ከቀረበ በኋላም ምርጫ ቦርድ የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው።
አጠቃላይ የይውረድልን ጥያቄው ሙሉ በሙሉ መስፈርቱን አሟልቶ የሚቀርብና ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነም የምርጫ ቦርዱ የይውረድልን ምርጫ አፈጻጸም ሂደቱን የሚያከናውን ይሆናልም ተብሏል።
በውይይቱ ላይ የታደሙ የፖለቲካ ፖርቲ አመራሮችም በረቂቅ መመሪያው ላይ ያላቸውን አስተያየቶችና ጥያቄዎች ለቦርዱ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
የቦርዱ ረቂቅ መመሪያ በ7 ምዕራፎችና በ41 አንቀጾች የተደራጀ ነው ተብሏል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!