የሀገር ውስጥ ዜና

413 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ከጅቡቲ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

By Melaku Gedif

October 11, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 413 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ከጅቡቲ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት ወደ ሀገራቸው ከተመለሱት ፍልሰተኞች ውስጥ 164 ሴቶች ሲሆኑ 249ቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው ተብሏል፡፡

ፍልሰተኞቹ በብዛት በጅቡቲ ታጁራ አካባቢ የነበሩ እና በሕገ-ወጥ ፍልሰት ምክንያት በስፍራው ሲሰቃዩ የቆዩ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡

የጅቡቲ-የመን መንገድ አደገኝነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ለበርካቶች የአካል ጉዳት፣ የሕመም፣ የዝርፊያ፣ የጾታዊ ጥቃትና የሞት መንገድ እየሆነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ስለሆነም ዜጎች ከስደት የሚመጣውን ስቃይ እና የዕድሜ ልክ ጠባሳ በመረዳት ሕገ-ወጥ ስደት በምንም አይነት መልኩ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ሊረዱ እንደሚገባ ኤምባሲው አሳስቧል፡፡

ዜጎችን ከመሰል አደጋ ለመጠበቅና ትውልድን ለመታደግም በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡