የሀገር ውስጥ ዜና

በሱዳን ያሉ ዜጎችን የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመለከተ

By ዮሐንስ ደርበው

October 11, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን በተከሰተው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡

በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ከጦርነት ቀጣናው ለማስወጣት የተቋቋመው ብሔራዊ ግብረ- ኃይል ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ በቀጣይ በሚሰሩ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡

የግብረ- ኃይሉ ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ÷ በሱዳን የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ ከ33 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

በድንበር አካባቢም አስፈላጊው የዜጎች አገልግሎት እንዲሰጣቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡

በቀጣይም በሱዳን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለማስወጣት ግብረ-ኃይሉ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

መነሻውን ካርቱም አድርጎ የሚከናወነው ዜጎችን የማስወጣት ሥራ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡