የሀገር ውስጥ ዜና

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡት ወንድማማቾች

By Melaku Gedif

October 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅማ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የተፈጥሮ ሳይንስ መስክ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ወንድማማቾች ቦና ደጀኔ እና ሮብሰን ደጀኔ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል።

የመልቀቂያ ፈተናውን ቦና ደጀኔ 566 ሲያዝመዘግብ÷ ሮብሰን ደጀኔ ደግሞ 537 ማስመዝገብ ችሏል፡፡

ከአንድ ቤተሰብ የተሻለ ውጤት ያመጡት ወንድማማቾቹ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳይነጣጠሉ በአንድ ክፍል በአብሮነት መከታተላቸውን ይናገራሉ፡፡

ይህ ሁኔታም በመማር ማስተማር ሒደቱ ያልገባቸውን ጉዳይ እርስ በርስ የመጠያየቅ እና የመረዳዳት ልምዳቸውን እንዳሳደገላቸው ነው የሚገልጹት፡፡

ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በመረዳዳት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸው ለተሻለ ውጤት እንዳበቃቸውም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

እናታቸው መምህርት መሰረት መስፍን እና አባታቸው ደጀኔ ሁርጌ በበኩላቸው÷ ልጆቻቸው ትምህርታቸው ላይ ትኩረት አድረገው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉ አንስተዋል፡፡

በመካከላቸው የ1 ዓመት ከ8 ወር የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ወንድማማቾቹ ቦና ደጀኔ እና ሮብሰን ደጀኔ እንደ ታላቅና ታናሽነታችው፣ በክፍል ተበላልጠው ከመማር ይልቅ ከሥር ጀምሮ አብረው እያጠኑ በአንድ ክፍል መማራቸው አሁን ላመጡት ውጤት አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በወርቃፈራው ያለው