የሀገር ውስጥ ዜና

ጀርመን ለኢትዮጵያ የ10 ነጥብ 1 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገች

By Meseret Awoke

October 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የ10 ነጥብ 1ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርጋለች፡፡

ድጋፉን በአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች ተግባራዊ ለማድረግ የጀርመን ኤምባሲ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ የተመድ የልማት ፕሮግራም ስምምነት ተፈራርመዋል፡

ስምምነቱን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አውየር እና የዩኤንዲፒ በኢትዮጵያ ተወካይ ቱርሃን ሳሌህ ናቸው የተፈራረሙት፡፡

ለሦስቱ ክልሎች የሚደረገው ድጋፍ በግጭቱ የተጎዱ ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱና የሰላም ግንባታን ለመደገፍ የሚውል ነው ተብሏል፡፡

የዩኤንዲፒ የሰላም ድጋፍ ማረጋጋት መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ሰፊ የማገገም እና የመልሶ ግንባታ ማዕቀፍ ውስጥ የተካተተ ነው መባሉን የተቋሙ መረጃ ያመላክታል፡፡