የሀገር ውስጥ ዜና

ለ7 ነጥብ 3 ሚሊየን ወገኖች የምግብና የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

By Meseret Awoke

October 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 7 ነጥብ 3 ሚሊየን ወገኖች የምግብና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ በሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታ፣ የአስቸኳይ ድጋፍ፣ የግብርና ስራዎችና ሌሎች ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

738 ሺህ 607 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፤ የቅድሚያ ቅድሚ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በድጋፍ መልክ እንዲደርሳቸው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።

በዚህም በአጠቃላይ ድጋፍ እንዲደርስ ከሚያስፈልጋቸው ውስጥ ወደ 7 ነጥብ 3 ሚሊየን ወገኖች ድጋፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ከሰላና ጸጥታ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ የአማራ ክልል በአንጻራዊነት ወደተሟላ ሰላም እየተመለሰ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በአንዳንድ ቦታዎች አልፎ አልፎ የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች ቢኖሩም አዲሱ አመራር አደረጃጀቱን እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እየዘረጋ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የተለያዩ ጥያቄዎችን በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት የሚቻለው መዋቅር በፍጥነት ማደረጀት ሲቻል ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በግብርና መስክ የአንበጣ መንጋን የመከላከል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ እና ነገ የሚከበረውን የብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ቀን በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር አብራርተዋል።

እንዲሁም የሀገር አቀፉ ቱሪዝም ኤግዚቢሽን ኢትዮጵያንና መስህቦቿን በአንድ ቦታ የያዘ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ተገኝቶ እንዲጎበኝ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።

በአመለወርቅ ደምሰው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!