የሀገር ውስጥ ዜና

የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት ጀመረ

By Melaku Gedif

October 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የተርባይኑ ጥገና ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን የጣቢያው ስራ አስኪያጅ ብሩክ ኤባ ገለጹ።

የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ስራ አስኪያጅ ብሩክ ኤባ፤ አሁን ላይ የኃይል ማመንጫ ተርባይኑ በመጠገኑ በሙሉ አቅሙ ሃይል በማመንጨት ላይ ነው ብለዋል።

ከጥር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ የኃይል ማመንጫ ተርባይኑ ላይ መጠነኛ ብልሽት ገጥሞት ከአንድ አመት በላይ ኃይል የማመንጨት ስራውን አቋርጦ እንደነበር አስታውሰዋል።

የኃይል ማመንጫ ተርባይኑን ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት የመለዋወጫ እጥረት ገጥሞ የነበረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከመስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ግን ተርባይኑ ተጠግኖ በሙሉ አቅሙ ኃይል እያመነጨ ነው ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር በመዲናዋ በቀን በአማካይ ከሚሰበሰበው 2 ሺህ 500ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ 1 ሺህ 280 ቶኑን እንዲቃጠል እያደረገ ይገኛልም ብለዋል።

“ረጲ” የሃይል ማመንጫ ዋና ዓላማው ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት ቢሆንም በተጓዳኝ ደግሞ ከተማን ፅዱ በማድረግ በቀን 1 ሺህ 280 ቶን ቆሻሻ ተቀብሎ ያቃጥላል ተብሎ እንደሚታሰብም ነው የገለጹት፡፡

በ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የተገነባው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ 2011 ዓ.ም በሙከራ ደረጃ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ እንደሚታወስ ኢዜአ በዘገባው አመልክቷል።