የሀገር ውስጥ ዜና

መንግስት የቤት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ለባለሃብቶች ድጋፍ እያደረገ ነው- ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

By Melaku Gedif

October 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የቤት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የኢሌሌ ግራንድ ሪል ስቴትን በዛሬው ዕለት መርቀው ከፍተዋል፡፡

ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ መንግስት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሃብቶች ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የኢሌሌ ግራንድ ሪል ስቴት ባለቤት ገምሹ በየነ በበኩላቸው÷ የሪል ስቴት ሽያጩ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው÷ ዜጎች አዲስ ሃሳብ የማመንጨት ልምዳቸውን እንዲያዳብሩም ጠይቀዋል፡፡

የኢሌሌ ግራንድ ሪል ስቴት በ9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን÷ከ1 ሺህ 400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል፡፡

በምስክር ተስፋዬ