የሀገር ውስጥ ዜና

የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ክልሎች ተከበረ

By Melaku Gedif

October 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 16ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ክልሎች ተከብሯል፡፡

ቀኑ “የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና ለሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው፡፡

በጋምቤላ ክልል የሰንደቅ ዓላማ ቀን የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር ተንኩዌይ ጆክ እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡

አቶ ተንኩዌይ ጆክ÷የውጭ ወራሪዎች የሀገራችንን ሉዓላዊነት ደፍረው ሲገቡ አባቶቻችን የአንድነታችንና የነፃነታችን ተምሳሌት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ድል አድርገዋል ብለዋል።

ሰንደቅ ዓላማችን በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ታሪክ የሰሩ ጀግኖቻችንና የፀጥታ ሃይሎቻችን ታላቅ ክብር ይገባቸዋል ሲሉም አውስተዋል፡፡

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 16ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በሆሳዕና ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡

አቶ እንዳሻው÷ የዘንድሮውን የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብር በሀገራችን የጀመርናቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ለማስፋት እና ያሉንን ሀብቶች በመገንዘብ ለላቀ ተጠቃሚነት የምንተጋበት ነው ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር ቃላችንን የምናድስበት፣ የምንከባበርበት ከተለያዩ ችግሮቻችን ፈጥነን የምንወጣበት፣ የህዝባችንን ተጠቃሚነት የምናረጋግጥበት፣ የህግ የበላይነትን የምናሰፍንበት ኢትዮጵያን የምናሻግርበትን እድል ይፈጥራል ብለዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም የሰንደቅ ዓላማ ቀን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰንና የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ተመስገን ዲሳሳ (ዶ/ር) በተገኙበት በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡

በተያያዘም በሐረሪ ክልል የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላምን ጨምሮ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ አፈጉባኤ አቶ ሙህኤዲን አህመድ በተገኙበት የሰንደቅ አላማ ቀን ተከብሯል።

የዘንድሮው የሰንደቅ አላማ ቀን ሀገራችን የተቃጣባትን ጥቃት ባሸነፈበት ማግስት መከበሩ ለየት እንደሚያደርገው የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የብልፅግና መንገድ ለማረጋገጥ ጠንክሮ በመስራት የሀገር ፍቅር መግለፅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በበዓሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በኢዮናዳብ አንዱዓለም፤ ተጨማሪ መረጃ ከክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮዎች

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!