አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሦስት ወራት ከ35 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ጥናትና ፕሮሞሽን ቡድን መሪ አበራ መንግስቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ በሩብ ዓመቱ ለ125 ባለሃብቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ እስካሁን ለ113ቱ ፈቃድ መስጠት ተችሏል፡፡
ባለሃብቶቹ በአምራች አንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት ባቀረቡት እቅድ መሰረት ፈቃድ መሰጠቱንም ነው የተናገሩት።
ባለሃብቶቹ ወደ ስራ ሲገቡም ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በየዓመቱ የሚከበረው ‘የናፍቆት ድሬ ሳምንት’ በአስተዳደሩ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በሚገባ ለማስተዋወቅ እድል በመፍጠሩ የአልሚዎች ቁጥር እየጨመረ እንደመጣም ጠቁመዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡
በተሾመ ኃይሉ