የሀገር ውስጥ ዜና

በጅግጅጋ በእሳት አደጋ ንብረታቸው ለወደመባቸው ነጋዴዎች ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

By Feven Bishaw

October 17, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በጅግጅጋ ከተማ ታይዋን የገበያ ማእከል በደረሰው የእሳት አደጋ ንብረት ለወደመባቸው ወገኖች በ2ተኛ ዙር ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፉ በገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው ከተለያዩ አካላት የተሰበሰበ ሲሆን÷ ለ 339 ተጎጂዎች በተቋቋመው ኮሚቴ በኩል እንደወደመባቸው ንብረት ሁኔታ በመደልደል ነው 100 ሚሊየን 872 ሺህ 497 ብር እንዲከፋፈል የተደረገው።

በመጀሪያው ዙር ድጋፍ በእሳት አደጋው የደረሰባቸው ውድመት ከ100 ሺህ ብር በታች ለሆኑ ሙሉ በሙሉ ክፍያ የተፈፀመላቸው መሆኑ የተገለፀ ሲሆን÷ በዛሬው 2ተኛ ዙር ድጋፍ እንደ ወደመባቸው ንብረት ከ10 በመቶ እስከ 50 በመቶ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ተብሏል።

በስነ-ስርአቱ ላይ በአሜሪካ፣ኖርዌይና ደቡብ ሱዳን የሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራ ተወካዮች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡