አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 7 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንድ በፈረንጆቹ 2040 የጠፈር ተመራማሪ ወደ ጨረቃ ለመላክ አቅዳለች ሲል የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል።
ሀገሪቱ በፈረንጆቹ 2035 የጠፈር ጣቢያ የመገንባት እቅድን እንዳላትም አስታውቃለች።
በትናንትናው ዕለት ሀገሪቱ የያዘቻቸውን ዕቅዶች ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ተመራማሪዎች ወደ ቬኑስ እና ማርስ በሚኖራቸው ተልዕኮ ላይ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
በፈረንጆቹ ነሐሴ ወር ህንድ የጠፈር መንኮራኩር በጨረቃ ደቡባዊ ጠረፍ ላይ በማሳረፍ የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን፥ በመስከረም ወር ደግሞ ፀሀይን ለማጥናት ሮኬት ማስወንጨፏ ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም የህንድ የጠፈር ምርምር ድርጅት (አይ ኤስ አር ኦ) ሰራተኞችን ወደ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኝ ምህዋር ለመላክ እና በሰላም ወደ ህንድ የውሃ አካል እንዲያርፉ የማድረግ ዓላማ ባለው የጋጋንያን ፕሮጀክት ላይ እየሰራ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
የፊታችን ቅዳሜም የጠፈር ምርምር ተቋሙ በተልዕኮው ዙሪያ ሙከራ እንደሚያካሂድም ነው የገለጸው።
ከፈረንጆቹ 2024 መጨረሻ ቀደም ብሎ ሰዎችን ይዞ ወደ ጠፈር ጉዞ ከመደረጉ በፊት የሙከራ በረራ በሮቦቶች እንደሚካሄድም ተገልጿል።