በሻንግሀይ በነበረው ጉብኝት የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም ልምድ መቅሰም ተችሏል – ቢልለኔ ስዩም
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቻይና ሻንግሀይ ከተማ በነበራቸው ቆይታ ስለ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ልምድ መቅሰምና መማር እንደተቻለ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቻይና ሻንግሀይ የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ቢልለኔ ስዩም በማብራሪያቸውም÷ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካቸው ሻንግሀይ ከተማ ላይ በተለያዩ ቦታዎች የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን በመግለጽ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው የሻንጋይ ስቶክ ገበያ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያም በቅርብ ጊዜ የተቋቋመ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን እንደለ ጠቅሰው ÷ በተለይ የሻንጋይ ስቶክ ገበያ በዓለም ከሚታወቁት መካከል አንዱ እንደመሆኑ መጠን ቦታው ላይ ልምድ መቅሰምና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ማየት ተችሏል ብለዋል፡፡
የሻንጋይ ስቶክ ገበያ 2 ሺህ የሚደርሱ ኩባንያዎችን አካቶ የሚሄድ አካል ነው ያሉት ኃላፊዋ÷ ይሄ ለእኛ ጥሩ ተሞክሮ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በተለይ ከቻይና ጋር ብዙ የሚያቀራርቡን ነገሮች ስላሉ እንደታዳጊ ሀገር ብዙ ልንማርበት እንችላለን ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁዋዌ የሻንጋይ ማዕከልን እንደጎበኙ ጠቅሰው÷ ተቋሙ በኢትዮጵያ በርካታ ፕሮጀክቶችና ኢንቨስትመንቶች እንዳሉት አስረድተዋል፡፡
በተለይም በቴሌኮም ዘርፉ ላይ እገዛ እያደረገ እንዳሉ በመግለጽ ኢትዮጵያ ከነደፈችው የዲጂታል ስትራቴጂ 2025 ተብሎ ከሚታወቀው ጋር ተቆራኝቶ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
በማዕከላቸው ላይ አዳዲሶቹ ቴክኖሎጂዎች ምንድናቸው የሚለውንም በመጎብኝት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ነገሮችን ለመረዳት እንደቻሉም አንስተዋል፡፡
በሀገራቱ መካከል የሁለትዮሽ ውይይት መካሄዱን ገልጸው ÷ ሻንጋይ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና የምትጫወት ከተማ እንደመሆኗ መጠን ከአዲስ አበባ ጋርም ምን ልምምድ ሊፈጠር ይችላል በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ውይይት መካሄዱን አስታውሰዋል፡፡
እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሻንጋይ የያንግሻን ወደብ ላይ ጉብኝታቸውን በማድረግ እንዳጠናቀቁ ቢልለኔ ስዩም በማብራሪያቸው ገልጸዋል፡፡
ወደቡ ቻይና ውስጥ ትልቅ የሚባለውና ብዙ ኮንቲነሮችን የሚያስተናግድ እንዲሁም የቤልት ኤንድ ሮድም አንድ አካል መሆኑን ጠቅሰው÷ በቴክኖሎጂም የታገዘ ትልቅ ወደብ ስለሆነ ከዚህ ብዙ ነገር ልንማርበት ችለናል ብለዋል፡፡