ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአሜሪካ ጦር በእስራኤል አቅራቢያ ሚሳኤሎችና ድሮኖችን መትቶ መጣሉ ተሰማ

By Melaku Gedif

October 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ጦር ሶስት ሚሳኤሎች እና በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በእስራኤል አቅራቢያ መትቶ መጣሉን አስታውቋል፡፡

የፔንታገን ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀኔራል ፓት ራይደር፥ ሚሳኤሎች እና ድሮኖች በሁቲ አማጽያን ቁጥጥር ስር ከሚገኙ የየመን ግዛቶች የተተኮሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጦር መሳሪያዎቹ በቀይ ባህር ወደ ሰሜን አቅጣጫ መተኮሳቸውን በመጥቀስም፥ ኢላማቸው በአመዛኙ እስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸም እንደነበር አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዘመናዊው የአሜሪካ ጦር መርከብ ከሃውቲ አማጽያን የተተኮሱ ሶስት ሚሳኤሎእ እና በርካታ ሰው አልባ አውሮላኖችን አላማቸውን ሳያሳኩ መትቶ መጣሉን ገልጸዋል፡፡

በሃማስ እና እስራኤል መካከል የተጀመረው ጦርነት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ በቅርቡ አሜሪካ ተጨማሪ ጦር ወደ እስራኤል ማስጠጋቷን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል፡፡

በሌላ በኩል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከነጩ ቤተ መንግስት በሰጡት መግለጫ÷ ዋሺንግተን ሐማስ እና ሩሲያ እንዲያሸንፉ አትፈቅድም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ባይደን አክለውም እስራኤል እና ዩክሬን የገቡበትን ጦርነት በአሸናፊነት እንዲያጠናቅቁ ኮንግረሱን በቢሊየን የሚቆጠር የድጋፍ ገንዘብ እንደሚጠይቁ ጠቁመዋል፡፡