አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማንኛውም ተለዋዋጭ ዓለማዊ ሁኔታ ፀንቶ ወደሚቆይ ስትራቴጂያዊ አጋርነት መሸጋገሩ በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪክ እንደ አንድ ከፍታ የሚታይ ነው ሲሉ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ተናገሩ፡፡
አምባሳደሩ በኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ÷ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከተፎካካሪነት ይልቅ አጋርነት ላይ የሚመሰረት መሆኑን አንስተዋል።
ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸው በሁሉም መስክ (ከኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በወታደራዊ እና በፀጥታ መስክ) መሆኑን ገልፀው፤ የሀገራቱ ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ከሚባሉት የግንኙነት አይነቶች ቀጥሎ የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡
በዓለም ላይ አራት ሃገራት ብቻ ከቻይና ጋር ይህን መሰል የግንኙነት ደረጃ ላይ እንዳሉ ጠቅሰው፤ በአፍሪካ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ በዚህ ደረጃ ከቻይና ጋር ግንኙነት የመሰረተች ሀገር መሆኗን አንስተዋል፡፡
ይህም ለኢትዮጵያ ሰፊ የኢኮኖሚ ትብብር ዕድል፣ የወታደራዊና የፀጥታ መስክ ትብብር፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የተቋማት ለተቋማት ግንኙነት፣ የኩባንያዎች ለኩባንያዎች ግንኙነት ከሸቀጥ ለሸቀጥ እና ከቁሶች ልውውጥ ባሻገር በአስተሳሰብ መቀራረብን የሚያመጣ ነው ብለውታል፡፡
ለሁለቱ ሀገራት እኩልና ፍትሃዊ ግንኙነት እንዲሁም በመከባበር ላይ ለተመሰረተ ግንኙነት ጥልቅ እድል ይዞ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል ብለዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር በበኩላቸው የኢትዮ-ቻይና የኢንቨስትመንት ፎረምን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ በቤጂንግና በሻንሀይ ከተማ የተካሄደው ፎረም ዓላማው ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ማስተዋወቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ማግባባት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በፎረሙ ላይ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ-ነዋያቸውን ለማፍሰስ የወሰኑ አምስት የቻይና ኩባንያዎች ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውንም አንስተዋል፡፡
እንዲሁም ወደ ስፍራው ካቀናው ልዑክ ጋር የአንድ ለአንድ ውይይቶች መደረጉን ጠቅሰው፤ ፎረሙ ውጤታማና የተሳካ መሆኑን ነው አምባሳደር ደዋኖ የተናገሩት፡፡