የሀገር ውስጥ ዜና

ለውጭ ዜጎች በጉቦ ፓስፖርት በመስጠት ሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 28 ሰዎች ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

By ዮሐንስ ደርበው

October 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለውጭ ሀገር ዜጎች በጉቦ ፓስፖርት በመስጠት ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 28 ተጠርጣሪዎች ላይ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ።

የምርመራ የማጣሪያ ጊዜውን የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ መደበኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ÷ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ገምበታ እና ምክትል ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ቦጋለን ጨምሮ በተቋሙ ሲሠሩ  የነበሩ 28 ግለሰቦች ናቸው።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አራቱ  ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከትናንት በስቲያ የፌደራል ፖሊስ  ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዘርፍ መርማሪ ÷ ተጠርጣሪዎቹ ከግለሰብና ከደላላ ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከ10 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር የሚደርስ ጉቦ በመቀበል ከሕጋዊ አሠራር ውጪ ለውጭ ሀገር ዜጎች ያልተገባ ፓስፖርት በመስጠት፣ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡትን በማጉላላት፣ በሀገር ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረስ፣ በመኖሪያ ቤት ሊገኙ የማይገባ የተቋሙ ሠነዶች በቤታቸው በመገኘታቸው እና ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ጠቅሶ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግና ማስረጃ ለመሰብሰብ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ችሎቱን መጠየቁ ይታወሳል፡፡

ጠበቆችም በደንበኞቻቸው ላይ ፖሊስ ያቀረበው የጥርጣሬ መነሻ ላይ ማን ከማን ጋር ገንዘብ ተቀበለ፣ ለማንስ ፓስፖርት ሰጠ የሚል የተናጠል የወንጀል ተሳትፎ  ተለይቶ ባልቀረበበት ሁኔታ ላይ በጅምላ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁ አግባብ አይደለም የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦችን አንስተው መከራከራቸው ይታወቃል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የረጅም ጊዜ ክትትል ተደርጎ በደኅንነት ተቋም ተይዘዋል ተብሎ በፖሊስ መገለጹ በራሱ ቀድሞ የምርመራ ሥራ መከናወኑን ያሳያል በማለት ደንበኞቻቸው ለተጨማሪ ጊዜ በእስር ሊቆዩ የሚችሉበት ምክንያት ሊኖር አይችልም ሲሉ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ችሎቱን ጠይቀው ነበር።

መርማሪ ፖሊስ የተናጠል ተሳትፏቸው ያልተገለጸው የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ የኦዲት ሪፖርት ገና ያልመጣ መሆኑን ተከትሎ ተሳትፏቸውን መግለጽ ያልቻለበትን ምክንያት ጠቅሶ በወቅቱ መልስ መስጠቱም ይወሳል፡፡

የተጠርጣሪዎችን ቃልና የምስክሮችን ቃል የመቀበል ስራ እንዳልተከናወነ በማብራራት የጠየቀው  ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቆ ነበር።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ፖሊስ የመነሻ የምርመራ መዝገቡን ለችሎቱ እንዲያቀርብ በማድረግ አጠቃላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት በይደር ለከሰዓት በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ  ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂ ላይ የተቋም ማህተም ባለመካተቱ ብይን ሳይሰጥ  ለዛሬ እንዲያድር ተደርጓል።

ይሁንና ለዛሬ በድጋሚ በይደር በተቀጠረው ቀጠሮ መሰረት ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ ክርክሩን መርምሮ ተጠርጣሪዎቹ ከተጠረጠሩበት ወንጀል  አንጻር ተጨማሪ ማስረጃ እንዳይጠፋና ግብረአበር እንዳይሸሽ ታሳቢ በማድረግ የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ አድርጎታል።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ለተጨማሪ ማጣሪያ ምርመራ ለፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ  በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ደንበኞቻችን ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በመጣስ ወንጀለኛ ተብለው በጅምላ ተፈርጀው የተላለፉ ዘገባዎችን በሚመለከት ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ያቀረቡትን አቤቱታ በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎችን  በደፈናው ወንጀለኛ አድርጎ የዘገበ ማንኛውም ሚዲያ ማስተካከያ እንዲያደርጉ በሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በአንድ ተጠርጣሪ ላይ የሰብዓዊ መብት ተጥሷል ተብሎ የቀረበው በዝርዝር ተጠቅሶ በጽሑፍ እንዲቀርብ ታዟል።

ሚዲያን በሚመለከት የቀረቡ አቤቱታን መርምሮ በቀጣይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ገልጿል።

የምርመራ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለጥቅምት 21 ቀን ተቀጥሯል፡፡

በታሪክ አዱኛ