አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ባህሬን በንግድ እና ቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ተስማምተዋል፡፡
በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል ጽ/ቤት አምባሳደር ሽፈራው ገነቴ ከሀገሪቱ ግብርና እና ማዘጋጃ ቤት ሚኒስትር ዋኢል ቢን ናስር አል ሙባረክ (ኢ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይየታቸውም በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ትብብር ይበልጥ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች እና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ወደ ባህሬን መላክ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በትኩረት መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር ሽፈራው ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ከመሆኗ ባሻገር የተለያዩ የቅባት እህሎች፣ ቅመማ ቅመም እና ሌሎች የግብርና ምርቶች መገኛ መሆኗን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን፣ የእንስሳት ውጤቶችን፣ ቅመማ ቅመሞችንና ሌሎች ምርቶችን ወደ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ ገበያ እንደምትልክም ጠቅሰዋል፡፡
ሚኒስትሩ በበኩላቸው ባህሬን የኢትዮጵያን ግብርና ምርቶች እና የእንስሳት ውጤቶች የሚያስተዋውቁ መድረኮች እና አውደጥናት ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል፡፡
ሀገራቱ በንግድ እና ቱሪዝም ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ስምምነት ላይ መደረሱም ተጠቁሟል፡፡