ጤና

እየተስተዋለ ያለው የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ እንዳይስፋፋ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

By Meseret Awoke

October 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተስተዋለው የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ እንዳይስፋፋ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አሳስቧል።

የጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ መከሰታቸውን አረጋግጧል።

በሚኒስቴሩ የኮቪድ-19 ምላሽ ግብረ-ኃይል ዋና አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ማሴቦ እንዳሉት፥ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ ተከስቷል፡፡

የጤና ሚኒስቴና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን በ2 ሺህ ያህል ናሙናዎች ላይ ባደረጉት ምርመራም የበሽታውን መከሰት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

በሽታው ሕዝብ በሚበዛባቸው በተለይም ትምህርት ቤቶች፣ የገበያ ሥፍራዎች፣ የእምነት ቦታዎች በስፋት የመሠራጨት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በከተሞችና ከፍተኛ መቀራረብ ባለባቸው የመኖሪያ ሥፍራዎች ጭምር የመስፋፋት አዝማሚያ ሊኖረው እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

የትንፋሽ አቅም ማነስ፣ የሰውነት መቆረጣጠምና የድካም ስሜቶች ከሕመሙ ምልክቶች መካከል እንደሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

ቫይረሱ ሳምባ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥርበት ደረጃ ሲደርስ ሳል፣ ከፍተኛ የሆነ የትንፋሽ ማጠርና ሌሎች ምልክቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸው፥ ምልክቶቹ የታየበት ግለሰብ በአፋጣኝ በጤና ተቋማት ሕክምና ማግኘት እንዳለበትም መክረዋል።

ሕብረተሰቡ እጅ በመታጠብ አፍና አፍንጫን በመሸፈን በሽታውን በቀላሉ መከላከል እንደሚችል መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች በቂ እረፍት በመውሰድ፣ ፈሳሽና ትኩስ ነገሮች በመጠቀምና ተገቢውን ሕክምና በማግኘት ሥርጭቱ እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረ-ሃሳቦች በመተግበር፣ በርና መስኮቶችን በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር በማድረግ መከላከል እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡