የሀገር ውስጥ ዜና

የብልጽግና ጉዞን ለማሳለጥ አመራሩ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ መስራት ይኖርበታል – አቶ አረጋ ከበደ

By Meseret Awoke

October 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ጉዞን ለማሳለጥ በየደረጃው ያለው አመራር የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ በቁርጠኝነትና በአንድነት መስራት ይኖርበታል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ይህን ያሉት “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ እየተሰጠ ባለው የብልጽግና አመራር ስልጠና ላይ ማምሻውን ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

በዚሁ ወቅት እንዳሉትም ፥ የብልጽግና ፓርቲ መርህ በህብረ ብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ የጸና ሀገራዊ አንድነትን ማረጋገጥ ነው።

የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባትና፣ ዘላቂና ፈጣን ልማትን ማምጣት እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥም ዋናው ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ሀገራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ እኩይ እሳቤዎች ለሰላም እጦት ምክንያት መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

ችግሮችን ተቋቁሞ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ከዳር እንዲደርስ በየደረጃው ያለው አመራር የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነትና በአንድነት መንፈስ መስራት እንደሚገባው ገልጸዋል።

ለፓርቲው አመራሮች ለ10 ቀናት የተሰጠው ስልጠና የፓርቲውን መርህ፣ ዓላማና ግብ ተገንዝቦ አሁን የገጠሙ ችግሮችን በህብረ ብሔራዊ አንድነት ለመፍታት አቅም የፈጠረ ነው ሲሉም ነው የገለጹት።

ሰልጣኞችም ከህዝብ ፊት ሆነው በመምራት ሀገር አሁን ካጋጠማት ችግር ወጥታ ወደ ብልጽግና ማማ እንድትሸጋገር በቁርጠኝነት እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።

ለህዝብ ዘላቂ ተጠቃሚነት ተግተው እንዲሰሩ ርዕሰ መስተዳድሩ ማመላከታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በአፍራሽና እኩይ ተግባር የተሰማሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና የሰላም አማራጭን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

በባህር ዳር እና ደሴ የስልጠና ተሳታፊ አመራሮች ወደመጡበት ሲመለሱ ስለክልሉ ነባራዊ እውነታ አምባሳደር በመሆን የገጽታ ግንባታ ሥራ ሊሰሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

#Ethiopia #Bahirdar

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!