የሀገር ውስጥ ዜና

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት በተለያዩ መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች – በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር

By Melaku Gedif

October 23, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ አጋርነት የአገራቱን የትብብር አድማስ በማስፋት ይበልጥ እንዲጠናከር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት በቻይና ርዕሰ-መዲና ቤጂንግ በተካሄደው 3ኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ጉባዔ ላይ መሳተፋቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በመድረኩም ንግግር አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት አሁናዊ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም÷ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቻይና ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ሁኔታዎች ወደ ማይቀይሩት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማደጉን ያበሰረ ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት የጋራ የፖለቲካ መተማመን ያጠናከረ እንደሆነ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመሆኑም ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ አጋርነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር በቁርጠኝነት ትሰራለች ነው ያሉት አምባሳደሩ።

በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ፎረም በኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በመሰረተ ልማት ጤና ግብርና ሌሎችም ወሳኝ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።

በማህበራዊ መስኩ ሀገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስራቸውን በማጠናከር ይበልጥ ትብብራቸውን ማጠናከር እንደሚቻል አመልክተዋል።